ሁሉም አገልግሎቶች ለኢትዮጵያውያን ነጻ ናቸው

ተልዕኮ

ቤተሰብ ፍለጋ ወይም የኢትዮጵያ ጉዲፈቻ ትስስር ፤ በጉዲፈቻ ምክንያት የተለያዩ የቤተሰብ አባላትን የሚያገናኝ ድርጅት ሲሆን ለጉዲፈቻ ልጆች ለተፈጥሮ ወላጆችእንዲሁም ለጉዲፈቻ ወላጆች በጠለቀ መረዳትና በርኅራኄ የተሞላ የድጋፍ አገልግሎትን ይሰጣል፡፡ በድህረ ገፃችን ላይ ያለው የመረጃ ቋትም በመፈላለግ ላይ ባሉ የጉዲፈቻልጆች፤ የጉዲፈቻ ወላጆች እና የተፈጥሮ ወላጆች የሰፈረ የኢትዮጵያውያን የጉዲፈቻ መረጃ የሚያሳይ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ማደጐ ወይም ጉዲፈቻ ትስስር የተቋቋመው ኢትዮጵያዊያን እናቶችና አባቶች በውጪ ሀገር በጉዲፈቻነት ተሰጥተው ከሚኖሩ ልጆቻቸው ጋር እንዲገናኙ ነው፡፡ ይህ ለልጆቹም ሆነ ለወላጆቻቸው ሰላምን እንደሚሰጥ ተስፋ እናደርጋለን፡፡

እርስዎ ከቤተሰብ ፍለጋ – ኢትዮጲያን አዶብሽን ኮኔክሸን አገልግሎት ፈልገው ሲመጡ ድርጅቱ የሚከተላቸው ሂደቶች፡-

   1. ከእርሶዎ መረጃ ይወስድና የማፈላለጊያ የበይነ መረብ ገጽ ከፍቶ በዚያ ላይ መረጃዎን ይለቃል፡፡
   2. በአሜሪካ የሚገኙ የድርጅቱ ሰዎች በጉዲፈቻ የሰጡትን/ጧትን ልጅዎን/የቤተሰቦዎን አባል ወይም የልጆዎን/የቤተሰቦዎን አባል አሳዳጊ ቤተሰቦችን ያፈላልጋሉ፡፡
   3. በጉዲፈቻ የተወሰደ/ች ልጆዎ/የቤተሰቦዎ አባል ከተገኘ/ች እና ከ 18 ዓመት በታች ከሆነ/ች አሳዳጊ ቤተሰቦቹን/ቿን ያናግራል፡፡ እርሶዎ ግንኙነት ማድረግ እንዲሁም ስለ ልጆዎ/የቤተሰቦዎ አባል በየጊዜው አዳዲስ መረጃዎችን ማግኘት እንደሚፈልጉ ያሳውቃል፡፡ ነገር ግን በጉዲፈቻ የተወሰደ ልጀዎ/የቤተሰቦዎ አባል እድሜው/ዋ 18 ዓመት ወይም ከዚያ በላይ ከሆነ በቀጥታ ለእርሱ/ሷ ስለ እርሶዎ ያሳውቃል፡፡
   4. በጉዲፈቻ የሄደው ልጆዎ/የቤተሰቦዎ አባል ወይም አሳዳጊዎቹ ግንኙነት ለማድረግ ከተስማሙ መረጃ እና ፎቶ ከእነርሱ ተቀብሎ ለእርሶዎ ያደርሳል፡፡
   5. ፎቶዎችን እና መረጃዎችን ለእርሶዎ ሲያደርስ በጉዲፈቻ ለተወሰደው ልጆዎ/የቤተሰቦዎ አባል ወይም አሳዳጊ ቤተሰብ የሚደርስ ቃለ-መጠይቅ ክእርሶዎ ጋር ያደርጋል ፤በርካታ ፎቶዎችንም ይወስዳል፡፡
   6. ያደረገውን ቃለ-መጠይቅ እና የወሰዳቸውን ፎቶዎች በሪፖርት መልክ በጉዲፈቻ ለተወሰደው ልጆዎ/የቤተሰቦዎ አባል ወይም አሳዳጊ ቤተሰብ ያደርሳል፡፡ ድርጅቱ ይህን ካደረገ በኃላ ከእርሶዎ ጋር ግንኙነቱን መቀጠል ወይም አለመቀጠል በጉዲፈቻ የተወሰደው ልጆዎ/የቤተሰቦዎ አባል ወይም ልጁ/ልጅቷ ከ18 ዓመት በታች ከሆነ/ች የአሳዳጊ ቤተሰብ ውሳኔ እንደሆነ ልብ ይሏል፡፡

ይህንን ሂደት ለምን እንከተላለን? ድርጅቱ ይህንን ሂደት የሚከተለው ሂደቱ እርሶዎ በየጊዜው መረጃ እንዲያገኙ፤ በጉዲፈቻ የተወሰደው ልጆዎ/የቤተሰቦዎ አባል አሊያም አሳዳጊ ቤተሰቦች ደግሞ የልጁን/ቷን ሙሉ ታሪክ እንዲያውቁ ስለሚያስችል ነው፡፡ የአሳዳጊ ቤተሰብ አባላት አማርኛ ቋንቋ አይችሉም፡፡ የሚተረጉምላቸው ይፈልጋሉ፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ሂደቱ በጉዲፈቻ ለተወሰደው ልጆዎ/የቤተሰቦዎ አባል ወይም አሳዳጊ ቤተሰብ ስለ እርሶዎ ሙሉ መረጃ እንዲኖራቸው ጊዜ ይሰጣቸዋል፡፡

ስለ ቤተሰብ ፍለጋኢትዮጲያን አዶብሽን ኮኔክሽን ከኢትዮጲያውያን ቤተሰቦች ተደጋግመው የሚነሱ ጥያቄዎች ለኢትዮጲያውያን ቤተሰቦች የተዘጋጀ፡

የኢትዮጵያ ማደጐ ወይም ጉዲፈቻ ትስስርን ማን መሰረተው?

የሁለት ኢትዮጵያዊያን ልጆች እናት የሆኑት አሜሪካዊት ይህንን ድህረገጽ  እ.ኤ.ኣ በጃንዋሪ 2014 ወይም ጥር 2006 ዓ.ም ዘረጉ፡፡ ወ/ሮ አንድሪያ የአንዷን ልጅ ወላጅ እናት አፈላልገው እ.ኤ.አ በ2004 ወይም በ1996 ዓ.ም አገኙ፡፡ የሁለተኛውን ልጅ ቤተሰብ ለአስር ዓመታት እያፈላልጉ ቆይተዋል፡፡ መፈለጋቸውንም አያቆሙም፡፡

እንዴት ነው የሚሰራው?

ኢትዮጵያውያን ቤተሰቦችና የማደጐ (የጉዲፈቻ) ቤተሰቦች የልጃቸውን የማደጐ (የጉዲፈቻ) መረጃ ከምስል ጋር የመረጃ ቋታችን ውስጥ ያስገባሉ፡፡ ይህ የመረጃ ቋት ማንም ሰው ሊገለገልበት ይችላል፡፡ ቤተሰቦች እዚህ ውስጥ የልጃቸውን መረጃ መካተት እና አለመካተቱን መፈለግ ይችላሉ፡፡ አዳዲስ መረጃ በማንኛውም ጊዜ መጨመር ስለሚቻልም ድህረገፁን በየጊዜው መጎብኘት ያስፈልጋል፡፡

በአሁኑ ወቅት መፈለጊያውና የመረጃ ማስገቢያው ቋንቋ በእንግሊዘኛ ነው፡፡ ወደፊት ሙሉውን ድህረገፅ ለመተርጎም ተስፋ እናደርጋለን: ግን በጣም ውድ ነው፡፡ እንግሊዘኛ ማንበብ የማይችሉ ኢትዮጵያዊያን መረጃ ለማስገባት ወይም ለመፈለግ ቋንቋውን የሚችል ሰው ያስፈልጋቸዋል፡፡

ይሄ ስራ የተጀመረው እ.ኤ.ኣ በጃንዋሪ 2014 ወይም በጥር 2006ዓ.ም እንደመሆኑ መረጃ ለማጠራቀም ረጅም ጊዜ ይፈልጋል፡፡ ይህንን ድህረገጽ የሚጠቀሙ ሰዎች በትዕግስት እንዲከታተሉን እንጠይቃለን፡፡

ይህ ድህረ ገፅ በነፃ የሚያገኙት አገልግሎት ስለሆነ ማንም በኢትዮጵያ ማደጐ ጉዲፈቻትስስር ስም ገንዘብ ሊጠይቅዎ አይገባም፡፡ ከተጠየቁም ይጠቁሙን፡፡

Mother seeing photos

ስለ ቤተሰብ ፍለጋኢትዮጲያን አዶብሽን ኮኔክሽን ምንነት፡

ቤተሰብ ፍለጋ – ኢትዮጲያን አዶብሽን ኮኔክሽን በኢትዮጲያ እንዲሰራ በተሻሻለው የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች አዋጅ ቁጥር 1113/2011 ሕጋዊ ሰውነት ተሰቶት የተመዘገበ የውጪ የበጎ አድራጎት ድርጅት ሲሆን ዕርስ በዕርሳቸው የሚፈላለጉ ኢትዮጲያውያን ቤተሰቦች እና ከኢትዮጲያ በጉዲፈቻ የሄዱ ልጆች ያቀረቡትን የጉዲፈቻ መረጃ በበይነ መረብ ቋቱ ውስጥ ይዟል፡፡ ቋቱ ልክ በከተማ ውስጥ እንዳለ የማስታወቂያ ሰሌዳ ወይም በፖል ለይ እንደተለጠፈ ፖስተር ሊቆጠር ይችላል፡፡ ላለፉት በርካታ ዓመታት በአሜሪካ እና አውሮፓ ልክ አሁን ቤተሰብ ፍለጋ-ኢትዮጲያን አዶብሽን ኮኔክሽን ያለው ዐይነት ቋት በዓለም አቀፍ ጉዲፈቻ የተለያዩ ቤተሰቦችን ለማገናኘት ጥቅም ላይ ይውል እንደነበር ልብ ይሏል፡፡

ቤተሰብ ፍለጋ ኢትዮጲያን አዶብሽን ኮኔክሽን ልጆችን ወስደው በጉዲፈቻ ከሰጡ ተቋማት ጋር ተመሳሳይ ነው?

በፍጹም! ቤተሰብ ፍለጋ-ኢትዮጲያን አዶብሽን ኮኔክሽን ህጻናት ማሳደጊያ ወይም የጉዲፈቻ ወኪል/ኤጀንሲ አይደለም፡፡ ይህ የውጪ የበጎ አድራጎት ድርጅት ነጻ በሆኑ ነገር ግን የዓለም አቀፍ ጉዲፈቻ ጉዳይ በሚያሳስባቸው እና ከኢትዮጲያ በጉዲፈቻ የተወሰዱ ልጆች ኢትዮጲያ ውስጥ ካለው ታሪካቸው ጋር እንዲተዋወቁ በሚፈለጉ የውጪ ሰዎች የተቋቋመ ነው፡፡ በጉዲፈቻ የተወሰዱ ኢትዮጲያውያን ልጆች ታሪካቸውን ማወቅ ሀገራዊ፣ አህጉራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ሕጎች የሠጧቸው መብቶች መሆናቸውን ልብ ይሏል፡፡

በጉዲፈቻ ከሰጡት/ጧት ልጅ ጋር በተያያዘ የኢትዮጲያውያን ቤተሰቦች መብቶች ምንድናቸው?

ዓለም አቀፍ ጉዲፈቻ ልጅ አዲስ ወላጅ የሚያገኝበት/የምታገኝበት ሕጋዊ ሂደት ነው፡፡ የአንድ ልጅ የጉዲፈቻ ሂደት በተጠናቀቀበት ቅጽበት የሰጠው ቤተሰብ ከልጁ/ልጅቷ ጋር የተያያዙትን መብቶች ያጣል፡፡ ይህም ማለት ልጁን/ልጅቷን በጉዲፈቻ የወሰደው ቤተሰብ ልጁ/ልጅቷ 18 ዓመት እስኪሞላው/ት ድረስ ሙሉ መብት በዕርሱ/ሷ ለይ ይኖረዋል ማለት ነው፡፡ በጉዲፈቻ የተወሰደው/ችው ልጅ 18 ዓመት ከሞላው/ት በኃላ በቤተሰቡ/ቧ ጉዳይ የመወሰን መብትን ይጎናጸፋል/ትጎናጸፋለች፡፡

ቤተሰብ ፍለጋ ኢትዮጲያን አዶብሽን ኮኔክሽን በጉዲፈቻ የሄዱት ኢትዮጲያውያን ልጆች አድራሻ አለው?

ፈጽሞ የለውም!!! ልጆቹም የት እንዳሉ በጭራሽ አያውቅም፡፡ ድርጅቱ የሚያደርገው የሚከተለውን ነው፡፡ በጉዲፈቻ ስለተወሰዱት ልጆች እና ስለ ኢትዮጲያውያን ቤተሰቦቻቸው መረጃ ከራሳቸው ከኢትዮጲያውያን ቤተሰቦች ይወስዳል፡፡ ከዛም ይህንን መረጃ በድርጅቱ ቋት ውስጥ ይለቀዋል፡፡ የተለያዩ የጉዲፈቻ ወላጆች የትስስር መድረኮችን ተጠቅሞም ከኢትዮጲያውያን ቤተሰቦች የተገኘውን መረጃ ያሰራጫል፡፡ በዚህ መሃከል በጉዲፈቻ የተወሰደው/ችው ልጅ ወይም የጉዲፈቻ ወላጆች መረጃውን ተመልክተውት መገናኘት ከፈለጉ ድርጅቱን ያናግራሉ ማለት ነው፡፡ ድርጅቱም ከኢትዮጲያውያን ቤተሰቦች ጋር በማገናኘት ይረዳቸዋል፡፡ ሂደቱ በርግጥ በጣም የተራዘመ ነው፡፡ ለምሳሌ የጉዲፈቻ ወላጆች መረጃውን በቶሎ ላይመለከቱት ይችላሉ፡፡ ድርጅቱ የጉዲፈቻ ወላጆች ባይመለከቱት እንኳን የጉዲፈቻ ልጆች አድገው ይመለከቱታል ብሎ ያምናል፡፡

ቤተሰብ ፍለጋ ኢትዮጲያን አዶብሽን ኮኔክሽን ለአገልግሎት ያስከፍላል?

በፍጹም፡፡ ክፍያ የማያስከፈል የውጪ የበጎ አድራጎት ድርጅት ነው፡፡

እንዴት ነው ቤተሰብ ፍለጋ ኢትዮጲያን አዶብሽን ኮኔክሽንን ማግኘት የሚቻለው? ፍለጋውስ እንዴት ይጀመራል?

ድርጅቱ የተለያዩ የማህበራዊ መገናኛ ብዙሃን አማራጮች (ለምሳሌ ድረገጽ Ethiopianadoptionconnection.org ፣ ፌስቡክ እና ኢሜል [email protected]) ያሉት ሲሆን ኢትዮጲያውያን ቤተሰቦች መረጃቸውን ከነአድራሻቸው በነዚህ የማህበራዊ መገናኛ ብዙሃን አማራጮች ለይ ያስቀምጣሉ፡፡ የሚያስቀምጡት መረጃ የመረጃ አስቀማጩን ስም፣ በጉዲፈቻ የተወሰደውን/ችውን ልጅ ወላጅ እናት ስም፣ በጉዲፈቻ የተወሰደውን/ችውን ልጅ ስም እና የኢትዮጲያውያን ቤሰተቦችን ስልክ ቁጥር መያዝ አለበት፡፡ ከዛ የድርጅቱ ሶሻል ዎርከሮች መረጃቸውን ያስቀመጡ ኢትዮጲያውያን ቤተሰቦችን ደውለው በማግኘት ድርጅቱ መረጃ ለመሰብሰብ ባዘጋጀው ቅጽ መሰረት መረጃ ይሞላሉ፡፡ ይህም መረጃ በድርጀቱ ሂደት (ቋት) ውስጥ አልፎ በጉዲፈቻ የሄደው/ችው ልጅ ከተገኘ/ች ሶሻል ዎርከሩ የመልሶ ማገናኘቱን ሂደት ያከናውናል፡፡

Family Visit from Beteseb Felega

ቤተሰብ ፍለጋ ኢትዮጲያን አዶብሽን ኮኔክሽን መረጃ ለመሰብሰብ ባዘጋጀው ቅጽ ላይ ያሉትን ጥያቄዎች መመለስ ባልችልስ? ለምሳሌ ልጄ የት ሃገር እንደተወሰደ/ች ባላውቅ ወይም በየትኛው ድርጅት በኩል እንደሄደ/ች ባላውቅ?

አይስጉ!!! ቤተሰብ ፍለጋ – ኢትዮጲያን አዶብሽን ኮኔክሽን የመረጃ እጥረት ቢኖርም ልጆዎን ከማፈላለግ ወደኃላ አይልም፡፡ ባለው መረጃ ተጠቅሞ ልጆዎን ለማግኘት ይጥራል፡፡ አንዳንዴ እንደውም እርሶ (ኢትዮጲያዊ ቤተሰብ) የሚሰጡጥትን ውስን መረጃ ተጠቅሞ ተጨማሪ መረጃዎችን ያገኛል፡፡ ለምሳሌ ልጁ/ጅቷ በየትኛው የጉዲፈቻ አመቻች ድርጅት በኩል እንደሄደ/ች ቢያውቁ ቤተሰብ ፍለጋ – ኢትዮጲያን አዶብሽን ኮኔክሽን ይህንን መረጃ ተጠቅሞ ልጁ/ጅቷ የት ሀገር እንደሄደ/ች ሊያውቅ ይችላል፡፡

ልጄን በጉዲፈቻ በምሰጥበት ጊዜ የሃሰት መረጃ ሰጥቼስ ቢሆን? ለምሳሌ እድሜውን/ዋን ቀንሼ ሰጥቼ ቢሆን?

በጉዲፈቻ ሂደት ውስጥ በርካታ የሃሰት መረጃዎች እንደሚኖሩ ይታወቃል፡፡ በተለይ ከጉዲፈቻ ጋር በተያያዙ ነገሮች ላይ በጥሩም ይሁን በመጥፎ የሰሩ ሰዎች ይህንን አሳምረው ያውቁታል፡፡ እርሶም ልጆዎን ሲሰጡ የሃሰት መረጃ ሰጥተው ሊሆን ይችላል፡፡ አይጨነቁ፡፡ ቤተሰብ ፍለጋ -ኢትዮጲያን አዶብሽን ኮኔክሽን ይህን እንደጥፋት ቆጥሮ አይወቅሶትም፤ አይከሶትም፡፡ ዕድል ቀንቶት ከልጆ ጋር ወይም ከአሳዳጊ ወላጆቹ ጋር ከተገናኙ እውነታውን ያስረዳሉ፡፡ አንዳንዴ በጉዲፈቻ የሄዱ ልጆች ወይም ወላጆች በጉዲፈቻ ሂደቱ ጊዜ የተሰጠውን ሃሰተኛ መረጃ ባወቁ ጊዜ ሊከፉ ወይም ሊበሳጩ ይችላሉ፡፡ ቤተሰብ ፍለጋ – ኢትዮጲያን አዶብሽን ኮኔክሽን እንደዚህ አይነት ነገር ብዙ ጊዜ እንደሚፈጠር ለልጆቹ ወይም ለጉዲፈቻ ወላጆች በማስረዳት ይተባበራል፡፡ ከርሶ የሚጠበቀው ጉዲፈቻው በሚከናወንበት ጊዜ የሰጡትን የተሳሳተ መረጃ እና እውነተኛውን መረጃ ለኛ መስጠት ነው፡፡ ሁለቱም መረጃዎች ለፍለጋው ጥቅም አላቸው፡፡

ልጄን ጥዬስ ቢሆን?

ቤተሰብ ፍለጋ ሁኔታዎች አስገድዶዎት እንጂ ፈልገው እንዳልጣሉ ይረዳል፡፡ ኢትዮጲያ ውስጥ ወድቀው ተገኝተው፤ በጉዲፈቻ ወደ ውጪ ሃገር ወተው በዚህ ሰአት ወላጆቻቸውን እንድናፈላልግላቸው መረጃ የሰጡ በርካታ ኢትዮጲያውን ስላሉ እና የእርሶም ልጅ ከእነዚህ ልጆች መሃከል አንዱ ሊሆን ስለሚችል ለቤተሰብ ፍለጋ – ኢትዮጲያን አዶብሽን ኮኔክሽን መረጃዎትን ከላይ በተጠቀሱት የማህበራዊ መገናኛ ብዙሀን አድራሻዎች በኩል ይስጡ፡፡ ድርጅቱ በቻለው አቅም ይረዳዎታል፡፡

ልጄን አፈላልጉልኝ ብዬ መረጃ ከሰጠው ከምን ያክል ጊዜ በኃላ ከልጄ ጋር ቤተሰብ ፍለጋ ኢትዮጲያን አዶብሽን ኮኔክሽን ያገናኘኛል?

ከላይ እንደተጠቀሰው ቤተሰብ ፍለጋ – ኢትዮጲያን አዶብሽን ኮኔክሽን አፈላላጊ እንጂ በጉዲፈቻ የተወሰዱት ልጆች ወይም የጉዲፈቻ ወላጆቻቸው አድራሻ ያለው ድርጅት አይደለም፡፡ በፍለጋ ውስጥ ልጆቹን ወይም የጉዲፈቻ ወላጆቹን ሊያገኛቸውም ላያገኛቸውም ይችላል፡፡ በከፍተኛ ፍለጋ በአጭር ጊዜ ልጆቹን ባያገኛቸው እንኳን የፍለጋው መረጃ በድርጅቱ ቋት ውስጥ ስለሚቆይ አንድ ቀን በጉዲፈቻ የተወሰዱት ልጆች (አድገውም ቢሆን) ሊያዩት እንደሚችሉ ቤተሰብ ፍለጋ – ኢትዮጲያን አዶብሽን ኮኔክሽን ያምናል፡፡ በርግጥ ልጆቹ እስኪያድጉ እና በራሳቸው ቋቱን መመልከት እስኪችሉ ድረስ ጊዜ ሊወስድ ይችላል፡፡ በዚህም ሳቢያ ድርጅቱ ልጆቹን በእርግጠኝነት በዚህ ጊዜ አገኛቸዋለሁ ማለት አይችልም፡፡

ግን ልጆቹን ለማግኘት ለምን በጣም ከበደ?

የጉዲፈቻውን ሂደት ለማፋጠን ሲባል ብዙ ጊዜ የልጆች ታሪክ ተቀይሮ ነው በጉዲፈቻ የተላኩት፡፡ ለምሳሌ እናት እና አባት በሕይወት እያሉ ሞተዋል ተብሎ ወይም በፍቃድ የተሰጥን ልጅ ተጥሎ የተገኘ/ች ተብሎ፡፡ በዚህም ምክንያት የጉዲፈቻ ወላጆች እና ኢትዮጲያውያን ወላጆች ተመሳሳይ እና ትክክለኛ መረጃ አይኖራቸውም፡፡ የተለያዩ እና የተሳሳቱ መረጃዎች ያሏቸውን ሰዎች ማገናኘት ደግሞ ከባድ መሆኑ የማይታበል ሀቅ ነው፡፡

ቤተሰብ ፍለጋ ኢትዮጲያን አዶብሽን ኮኔክሽን ልጄን ቢያገኝልኝ ወዲያውኑ አድራሻውን/ዋን ይሰጠኛል?

ይሄ በጉዲፈቻ በተወሰዱት ልጆች ወይም በጉዲፈቻ ወላጆቻቸው የሚወሰን ነው፡፡ ድርጅቱ በአሜሪካም ተመዝግቦ የሚሰራ ሲሆን በውጭ ካሉበት ግዴታዎች መሀከል የጉዲፈቻ ወላጆችን እና በጉዲፈቻ የሄዱ ልጆችን የግለኝነት መብቶች ማክበር አንዱ ነው፡፡ ድርጅቱ የጉዲፈቻ ወላጆች እና በጉዲፈቻ የሄዱ ልጆች ለኢትዮጲያውያን ቤተሰቦች እንዲሰጥ የፈለጉትን ነገር በሙሉ ይሰጣል፡፡ አንዳንድ የጉዲፈቻ ወላጆች እና በጉዲፈቻ የሄዱ ልጆች አድራሻቸው ለኢትዮጲያውያን ቤተሰቦች እንዲሰጥ ይፈቅዳሉ፡፡ አንዳዶቹ ደግሞ አድራሻቸውን ከልክለው ግንኙነቱ በድርጅቱ በኩል ብቻ እንዲሆን ይፈልጋሉ፡፡ የተወሰኑ የጉዲፈቻ ወላጆች እና በጉዲፈቻ የሄዱ ልጆች ደግሞ ሁለቱንም መንገድ ይጠቀማሉ፡፡ ድርጅቱ ያለጉዲፈቻ ወላጆች እና በጉዲፈቻ የሄዱ ልጆች ፍቃድ አድራሻቸውን ለኢትዮጲያውያን ቤተሰቦች አይሰጠም፡፡ በህግ ያስጠይቀዋል፡፡ እዚህ ጋር ኢትዮጲያውያን ቤተሰቦች ማወቅ ያለባቸው ነገር የድርጅቱ ሶሻል ዎርከሮች እንኳን የጉዲፈቻ ወላጆች ወይም በጉዲፈቻ የሄዱት ልጆች አድራሻ አይኖራቸውም፡፡ የድርጅቱ የበላይ ሰዎች ብቻ ናቸው የጉዲፈቻ ወላጆች ወይም በጉዲፈቻ የሄዱት ልጆች አድራሻ የሚኖራቸው፡፡

ልጆቻችንን ካገኘ በኃላስ ለምን ድርጅቱ ስለልጆቻችን ወዲያውኑ መረጃዎችን አይሰጠንም?

ቤተሰብ ፍለጋ-ኢትዮጲያን አዶብሽን ኮኔክሽን በጉዲፈቻ የሄዱትን ልጆች አግኝቷቸዋል ማለት በግላዊ ህይወታቸው ውስጥ ገብቶ ይቆጣጠራቸዋል ማለት አይደለም፡፡ አንዳንድ የጉዲፈቻ ወላጆች እና በጉዲፈቻ የሄዱ ልጆች ከኢትዮጲያውያን ቤተሰቦች ጋር ላለው የግንኙነት ሂደት ተባባሪ አይሆኑም፡፡ ጨርሶ ግንኙነቱን ላይፈልጉትም ይችላሉ፡፡ ድርጅቱ የሚያደርገው ነገር፤ የጉዲፈቻ ወላጆችን ወይም በጉዲፈቻ የሄዱ ልጆችን እንዳገኛቸው፣ ለግንኙነቱ ፍቃደኛ መሆናቸውን ይጠይቃል፡፡ ፍቃደኛ ከሆኑ ስለ ኢትዮጲያውያን ወላጆች ያለውን መረጃ በሙሉ ይሰጣቸዋል፡፡ ኢትዮጲያውያን ወላጆችም እነሱን ለማግኘት ጓጉተው እየጠበቁ እንደሆነ ያሳውቃቸዋል፡፡ከኢትዮጲያውያን ወላጆች ጋርም መገናኘት እንዳለባቸው ሊያሳምናቸው ይጥራል፡ ፡ ከኢትዮጲያውያን ወላጆች ድብዳቤ ወስዶ ያደርሳል፡፡ ድርጅቱ ሁሉንም ጥረት አድርጎ የጉዲፈቻ ወላጆች ወይም በጉዲፈቻ የሄዱ ልጆች ለግንኙነቱ ፍቃደኛ ካልሆኑ ግን አያስገድዳቸውም፡፡ የማስገደድ ስልጣኑም የለውም፡፡ ቤተሰብ ፍለጋ-ኢትዮጲያን አዶብሽን ኮኔክሽን ተባባሪ ድርጅት እንጂ የህግ አካል አይደለም፡፡ በኢትዮጲያውን ቤተሰቦች እና በጉዲፈቻ በሰጧቸው ልጆች እና አሳዳጊ ወላጆቻቸው መሃከል ግንኙነቱ ሊቀጥል የሚችለው በጉዲፈቻ በሄዱት ልጆች ፍቃድ ወይም ልጆቹ ከ18 ዓመት በታች ከሆኑ በጉዲፈቻ ወላጆቻቸው ፍቃድ ብቻ ነው፡፡

የልጄን አድራሻ ቤተሰብ ፍለጋ ኢትዮጲያን አዶብሽን ኮኔክሽን አገኘው እንበል፡፡ ቀጣዩ ሂደት ምንድነው?

ተፈላጊው/ዋ ልጅ ከ18 ዓመት በላይ ከሆነ/ች በቀጥታ ራሱን/ሷን ከተጠቀሰው እድሜ በታች ከሆነ/ች ግን የጉዲፈቻ ወላጆቹን/ቿን ድርጅቱ ያናግራል፡፡ ካናገራ በኃላ በግንኙነቱ ዙሪያ እንዲወስኑ እድሉን ይሰጣቸዋል፡፡ በዚህ ጊዜ ተፈላጊው/ዋ ልጅ ወይም የጉዲፈቻ ወላጆች ስለግንኙነቱ የተለያዩ ውሳኔዎችን ሊያሳልፉ ይችላሉ፡፡ ከነዚህ ውሳኔዎች መሃከልም፡-

   • ከነጭራሹ ግንኙነቱን አንፈልገውም ሊሉ ይችላሉ፡፡ (ስለዚህ ጉዳይ ከታች በዝርዝር ተቀምጧል፡፡)
   • በድርጅቱ በኩል መልዕክት እየላክን ነገር ግን አድራሻችንን ሳንሰጥ ግንኙነቱን ማድረግ እንፈልጋለን ሊሉ ይችላሉ፡፡
   • በዓመት አንድ ጊዜ ብቻ ፎቶ እና መልዕክት እየላክን ግንኙነቱን ማድረግ እንፈልጋለን ሊሉ ይችላሉ፡፡
   • በቀጥታ በመደወል አሊያም መልዕክት በመላክ እንዲሁም በተለያዩ የማህበራዊ መገናኛ ብዙሃን አማራጮች (ኢሜል፣ ስካይፒ፣ ፌስቡክ) ግንኙነቱን ማድረግ እንፈልጋለን ሊሉ ይችላሉ፡፡
   • በአካል ኢትዮጲያ ተገኝቼ ኢትዮጲያውያን ቤተሰቦችን ማግኘት እፈልጋለሁ ሊሉ ይችላሉ፡፡

ልጄ ከተገኘ/ች ለምንድነው ማያዋራኝ/ማታዋራኝ?

ይህ እንደ ልጆቹ ዕድሜ የተለያየ መልስ ያለው ሲሆን፡-

A mother receiving photos from her child

በጉዲፈቻ የተወሰደው/ችው ልጅ በተገኘ/ች ሰአት ከ18 ዓመት በላይ ከሆነ/ች፡ሁኔታዎችን ለማመቻቸት ጊዜ ሊፈልጉ ይችላሉ፡፡ ምን አልባትም ኢትዮጲያውያን ቤተሰቦቻቸው እንደማይፈልጓቸው፣ እንደጣሏቸው አሊያም እንደሞቱ እየተነገራቸው ያደጉ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ በዚህም በድንገት ኢትዮጲያውያን ቤተሰቦቻቹ እየፈለጓችሁ ነው ሲባሉ ግራ ሊጋቡ ይችላሉ፡፡ ይህን ከግምት በማስገባት ኢትዮጲያውያን ቤተሰቦች ታጋሽ መሆን አለባቸው፡፡ ጊዜም ሊሰጧቸው ይገባል፡፡

በጉዲፈቻ የተወሰደው/ችው ልጅ በተገኘ/ች ሰአት ከ18 ዓመት በታች ከሆነ/ች፡ የጉዲፈቻ ወላጆቻቸው በልጆቹ ማንኛውም ጉዳይ ላይ ለመወሰን ሙሉ እና ህጋዊ መብት አላቸው፡፡ አንዳንድ ጊዜ የጉዲፈቻ ወላጆች ከኢትዮጲያውያን ቤተሰቦች ጋር መገናኘት ላይፈልጉ ይችላሉ፡፡ በጉዲፈቻ የወሰዷቸው ልጆችም ከስጋ ቤተሰቦቻቸው ጋር ግንኙነት እንዲፈጥሩ ላይፈልጉ ይችላሉ፡፡ ይህ በሚፈጠር ጊዜ ልጆቹ እስኪያድጉ እና በራሳቸው መወሰን የሚችሉበት ዕድሜ ላይ እስኪደርሱ ድረስ መጠበቅ ግድ ይላል፡፡

እንደአጠቃላይ መታወቅ ያለበት ነጥብ የጉዲፈቻ ወላጆች የፈጸሙት ጉዲፈቻ ዝግ እንደሆነ እና አንድ ጊዜ ልጆችን በጉዲፈቻ ከወሰዱ በኃላ ምንም አይነት የኢትጲያውያን ቤተሰቦች ግንኙነት እንደማይኖር ነው የሚያስቡት፡፡ ኢትዮጲያውያን ቤተሰቦች ከዕናንተ እና ከወሰዳቹአቸው ልጆች ጋር መገናኘት ይፈልጋሉ ሲባሉ ያልጠበቁት ስለሚሆን ሊፈሩ ይችላሉ፡፡

እንዳንዴ የልጆቻችን አድራሻ ኖሮን ስንደውል ወይም መልዕክት ስንልክ አይመልሱም፡፡ ይህ የማህበራዊ መገናኛ ብዙሃን መልዕክቶችንም ይጨምራል፡፡ ቤተሰብ ፍለጋ ኢትዮጲያን አዶብሽን ኮኔክሽን በዚህ ጉዳይ ላይ ምን ይላል?

ምዕራባውያን እና አሜሪካውያን በስራ በጣም የተጨናነቁ ናቸው፡፡ በዚህ የተነሳ በየዕለቱ ግንኙነት አይኖራቸውም፡፡ ብዙ ጊዜ ሁለቱም የጉዲፈቻ ወላጆች ስራ የሚሰሩ ሲሆን ልጆች ደግሞ ይማራሉ፤ ከትምህርት በኃላ በሚከናወኑ የስፖርት እና የመዝናኛ ተግባራት ላይም ይሳተፋሉ፡፡ በዚህም ከኢትዮጲያ ለሚላኩ ተደጋጋሚ መልዕክቶች እና የእናውራ ጥያቄዎች መመለስ አይችሉም፡፡ እንደውም ኢትዮጲያውያን ቤተሰቦች ካላወራን እና መልዕክቶቻችንን ካልመለሳቹ እያሉ ካስጨነቋቸው ግንኙነቱን ከነጭራሹ ሊያቆሙት ይችላሉ፡፡

የጉዲፈቻ ወላጆች ግንኙነት ላለማድረግ ከሚወስኑባቸው ምክኒያቶች መሃከል ዋነኞቹ የሚከተሉት ናቸው፡

   • ብዙ የጉዲፈቻ ወላጆች ጉዲፈቻውን በሚፈጽሙበት ጊዜ የልጆቹ ኢትዮጲያውያን ወላጆች እንደሞቱ ነው የተነገራቸው፡፡ በዚህም አሁን ሊያገኟቸው እየሞከሩ ያሉት ወላጆች አጭበርባሪዎች እንጂ እውነተኛ ወላጆች/ቤተሰቦች አይመስሏቸውም፡፡ ጥሩ የጉዲፈቻ ወላጆች ከሆኑ የ ዲ ኤን ኤ ምርመራ ያደርጋሉ፡፡
   • ብዙ የጉዲፈቻ ወላጆች ኢትዮጲያውያን ቤተሰቦች ገንዘብ እንጂ እውነተኛ ግንኙነት ፈልገው እንዳልመጡ ያስባሉ፡፡ በርግጥ ይሄ የሚሆነው በውጪ ያሉ የጉዲፈቻ ወኪል ድርጅቶች የኢትዮጲያውያን ቤተሰቦችን ስም በዚህ መንገድ ስለሚያጠፉ ነው፡፡ ከገንዘብ ጋር ተያይዞ በውጪ ባሉ የጉዲፈቻ ወኪል ድርጅቶች በጉዲፈቻ ወላጆች ላይ ስለ ኢትዮጲያውያን ቤተሰቦች የሚነዛው ወሬ መሰረተቢስ ሃሜት መሆኑን ቤተሰብ ፍለጋ – ኢትዮጲያን አዶብሽን ኮኔክሽን በጽኑ ያምናል፡፡
   • አንዳንድ የጉዲፈቻ ወላጆች ደግሞ ኢትዮጲያውያን ቤተሰቦች የጉዲፈቻውን ሂደት ካስኬደው ተቋም መረጃ እያገኙ እንደሆነ ይሰማቸዋል፡፡ ይሄም ግን ሌላው መሰረተቢስ ጉዳይ መሆኑን ቤተሰብ ፍለጋ-ኢትዮጲያን አዶብሽን ኮኔክሽን ያውቃል፡፡
   • የተወሰኑ የጉዲፈቻ ወላጆች ከኢትዮጲያውያን ቤተሰቦች ጋር ማውራት ህገ-ወጥ እንደሆነ ያስባሉ፡፡ ይሄም ሌላው በዓለም-አቀፍ የጉዲፈቻ ወኪል ድርጅቶች የተፈጠረ ውዥንብር ነው፡፡
   • አንዳንድ የጉዲፈቻ ወላጆች ደግሞ ኢትዮጲያውያን ቤተሰቦች ልጆቻችንን መልሱልን የሚል ጥያቄ ያነሳሉ የሚል ፍርሃት አላቸው፡፡